በአማራ ክልል ከእቅድ በላይ የቅባትና የጥራጥሬ ምርት ወደ ውጭ ተልኳል – ቢሮው
ባሕርዳር፤ ነሐሴ 1/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ከእቅድ በላይ የቅባትና የጥራጥሬ ምርት ወደ ውጭ መላኩን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የሰብልና ኢንዱስትሪ ምርቶች ግብይት ዳይሬክተር ልንገረው አበሻ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በግብርናው ዘርፍ ገበያ ተኮር የሆኑ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማስፋት እየተሰራ ነው።
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ስድስት ሚሊዮን 837ሺህ 447 ኩንታል የቅባትና የጥራጥሬ ምርት ወደ ውጭ በመላክ 665 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘት መቻሉን አስታውቀዋል።
ይህም በበጀት ዓመቱ ወደ ውጭ ለመላክ በዕቅድ ተይዞ ከነበረው ምርት ጋር ሲነጻጸር በአንድ ሚሊዮን 274ሺህ 173 ኩንታል ብልጫ እንዳለው አመላክተዋል።
ከተላከው ውስጥም ከሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት ሲሆን፤ ቀሪው ደግሞ ቦሎቄ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾ፣ ባቄላ፣ ኑግና ሌሎች ሰብሎች ናቸው ብለዋል።
ከዕቅድ በላይ ምርቱ ወደ ውጭ ሊላክ የቻለው በምርት ዘመኑ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በጥራትና በብዛት በማዘጋጀት ለገበያ በመቅረቡ እንደሆነ ገልጸዋል።
ላኪዎች በቀጥታ ከአርሶ አደሩና አምራች ባለሃብቶች ምርቱን በመሰብሰብ በወቅቱ ወደ ውጭ እንዲላክ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።
ይህም የአርሶ አደሩንና በማምረት ላይ የሚገኙ ባለሃብቶችን በግብይት ሰንሰለቱ ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለበት የበጀት ዓመት መሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ወደ ውጭ መላክ የተቻለውም ወደ ሩቅ ምስራቅ፣ እሲያ፣ አውሮፓና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መሆኑን ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ከስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱንም ጠቁመዋል።
